የጋርመንት ኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል ሊከፍት ነው

በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የኢንጂነሪንግና የቴክኖሎጂ ኮለጅ በያዝነው ዓመት ሁለተኛ ሰሚስተር የጋርመንት ኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል በመክፈት አዳዲስ ተማሪዎች እንደሚቀበል አሳወቀ፡፡

ኮሌጁ አዲሱን የትምህርት ክፍል በሚመለከት ያዘጋጀው ስርአተ ትምህርት ከውጭ ተቋም የመጡ ባለሙያዎች (external reviewers) ለመገምገም በአድዋ ከተማ በተካሄደው ብሔራዊ አውደ ጥናት እንደተገለፀው በኢትዮጵያ በጨርቃጨርቅ ፣ በአልባሳት ፣ በስፌትና በፋሽን ዲዛይን ዘርፎች እምቅ የጥሬ እቃና የገበያ አቅም ቢኖርም በዘርፉ የሚታየው የተማረ የሰው ሃይል እጥረት የሚፈለገው ገቢ እንዲናገኝ እንቅፋት ሆኗል፡፡

የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ዮሐንስ ብርሃነ ዘርፍ ያሉትን የትምህርትና የክህሎት ክፍተቶች በሚገባ በመለየት ችግሩን በመቅረፍ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ አክሱም ዩኒቨርሲቲ የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማበርከት ይህን ዲፓርትመንት እንደከፈተ ገልፀዋል፡፡ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ፕረዚዳንት ዶ/ር ፀሃዬ አስመላሽ በበኩላቸው ለአዲሱ ዲፓርትመንት የሚያስፈልጉ ግብአቶች ለሟሟላት የተለያዩ እቃዎች ግዥ ጨረታ እንዳወጣና ሂደቱን እየተከታተሉት እንደሆነ በመግለፅ የኮሌጁን እንቅስቃሴ አድንቀዋል፡፡

የብሔራዊ አውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች በተጨማሪ በአድዋ በሚገኘው አልመዳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ አቅራቢያ በመገንባት ያለው የቴክስታይልና ጋርመንት ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ሂደት ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡

በአድዋ የሚከፈተው አዲሱ ኮሌጅ ዩኒቨርሲቲው ያሉት ካምፓሶች ወደ አራት የሚያሳድግ ሲሆን ተማሪዎችም በፋብሪካው ያሉትን ማሺነሪዎች በቅርቦት በመጠቀም የተሻለ ክህሎት እንዲያገኙ እንደሚረዳ ይጠበቃል፡፡