አለም አቀፍ የሴቶች ቀን ማርች 8 “በተጠናከረ የሴቶች አደረጃጀት የሴቶች እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት እናረጋግጣለን“ በሚል መሪ ቃል በአክሱም ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከበረ ፡፡ በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የሴቶችና ወጣቶች ጉዳዮች ዳይሬክተር ወ/ሮ አበባ አሰፋ ባሰሙት ንግግር ማርች 8 ለአለም ሴቶች መነቃነቅ ፣ እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት በር የከፈተ ቀን መሆኑን ገልፀዉ በአገራችን ኢትዮጵያም በዚሁ በመነቃቃት ብዙ የሴቶች ንቅናቀዎችና አደረጃጀቶች እየተፈጠሩ ሴቶች በማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታዎች እየተመቻቹ ይገኛሉ ብለዋል ፡፡
ወ/ሮ አበባ አሰፋ አክለዉ የማርች 8 አላማዎች ለማሳካት አክሱም ዩኒቨርሲቲ በሴቶች ላይ በተለይ ደግሞ በሴት ተማሪዎች ዙርያ ላይ በርከት ያሉ ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝ ከነዚህም ዉስጥ የአቅም ግንባታ በመስጠት ፣ በኢኮኖሚ በመደገፍ ፣ የማበረታቻ ሽልማቶችን በመሸለም ፣ ሴት ተማሪዎች በመምህርነት እንዲቀጠሩ በማድረግ ሴቶች በትምህርታቸዉ ዉጤታማ እንዲሆኑና እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል ፡፡ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ኘሬዚዳንት ዶ/ር ፀሃዬ አስመላሽ በበኩላቸዉ በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር የሴት ተማሪዎች አስተዋፅኦ የላቀ መሆኑን ገልፀዉ አሁንም በሃይማኖት ፣ በብሄር ወዘተ ሳይለያዩ ሰላማቸዉንና መብቶቻቸዉን እንዲያስከብሩ ጠይቀዋል ፡፡