የጣልያን ወራሪ ጦር የተሸነፈበት 122ኛዉ የአድዋ ድል በዓል በአድዋ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከበረ ፡፡
በዓሉን ለመዘከር “ አድዋ በአብሮነት የአሸናፊነት ተምሳሌት ”በሚል በተዘጋጀ አዉደ ጥናት ላይ እንደተመለከተዉ የድሉን ታሪክ ከነ እሴቶች ለቀጣዩ ትዉልድ ለማስተላለፍ በመንግስት በኩል ህብረተሰቡን እና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላትን ያሳተፈ በሶስት ዘርፎች የተከፋፈለ ስራ በመስራት ላይ ነዉ ፡፡ ከነዚህም የፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ የመገንባት ስራ ቀዳሚዉ ሲሆን ሁለተኛዉ ለአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም መገንባት እንዲሁም በሶስተኛዉ ደረጃ የተያዘዉ አድዋን የቱሪስት መናሃርያ የማድረግ እንቅስቃሴ ነዉ ፡፡ በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የአርኮየሎጂና ቱሪዝም ኢንስቲትዮት ዳይሬክተር አቶ ተክለብርሃን ለገሰ Adwa Mounatains and Adwa Victory Tourism project የአድዋ ተራሮችና የአድዋ ጦርነት ድል ቱሪዝም ኘሮጀክት በሚል ርእስ ባቀረቡት ጥናት በአድዋና አከባቢዋ ባህላዊ እና ተፈጥሮአዊ ቅርሶች ዘላቂ የቱሪዝም ልማት በማካሄድ ከአስሩ ተመራጭ የኢትዮጵያ ቱሪዝም መዳረሻዎች አንድ ሆና ማየትን ራእይ ያደረገ አዳዲስ የቱሪዝም ምርቶች ያካተተ ኘሮጀክት መቀረፁን ይፋ አድርገዋል ፡፡
የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚዬም ግንባታ በሚመለከት ታዋቂዉ የታሪክ ተመራማሪ ኘሮፌሰር ባህሩ ዘዉዴ ባቀረቡት ፅሁፍ እስካሁን የኘሮጀክቱ የመነሻ ሃሳብ ዝግጅት ተካሂዶ ለሙዚየሙ አመቺ የሆነዉን ቦታ የመምረጥ ስራ ተከናዉኗል ፡፡ በዚህም መሰረት የሙዚየሙ ግንባታ የመጀመሪያዉ ጦርነት በተካሄደበት በተለምዶ ምንድብድብ በሚባለዉ ቦታ እንዲሆን መወሰኑን ገልፀዋል ፡፡