ዩንቨርሲቲው የአካባቢውን ማህበረሰብ የመረጃ ተደራሽነት ለማስፋት የሚያስችል የማህበረሰብ ሬድዮ ጣቢያ ሊያቋቁም ነው

አክሱም ዩንቨርስቲ የአካባቢውን ማህበረሰብ የመረጃ ተደራሽነት ዕድል ለማስፋት የሚያስችል የማህበረሰብ ሬድዮ ጣቢያ ለማቋቋም የቅድመ ዝግጅት ስራዎች  ማጠናቀቁን አስታወቀ፡፡

 ዩኒቨርሲቲው ይህንን ያስታወቀው ከዩኒቨርሲቲው ሁሉም ግቢዎች ፣ ከአክሱም ፣ ሽረና ዓድዋ የተወከሉ ከ 200 በላይ የማህበረሰቡ አባላት በተሳተፉበት የማህበረሰብ ሬድዮ ጣቢያው በበላይነት የሚመሩት የጠቅላላ ጉባኤ እና የቦርድ አባላት ምርጫ በተካሄደው ጉባዔ ላይ ነው፡፡

 የአክሱም ዩኒቨርስቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ፀሃየ አስመላሽ በጉባኤው እንደገለፁት  የማህበረሰብ ሬድዮው ስራ ሲጀምር በዩኒቨርሲቲው የተሰሩ የጥናትና ምርምር ውጤቶች በቀላሉ ወደ ህበረተሰቡ ለማድረስ ድርሻው የጎላ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የዩኒቨርስቲውን እንቅስቃሴ የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ እና የአካባቢውን ማህበረሰቡ በቀጥታ ተሳታፊ ለማድረግ እና  የአካባቢውን ህብረተሰብ ወቅታዊ እና ትክክለኛ መረጃ እንዲኖረው የማህበረሰብ ሬድዮው ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረዉም ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል፡፡

በጉባኤው ላይ የማህበረሰብ ሬድዮ ጣቢያውን ለማቋቋም ከተከናወኑ ስራዎች መካከል  የማህበረሰቡ ፍላጎት የሚያሳይ የዳሰሳ ጥናትና ሌሎች ቅድመ ስራዎች የተሰሩ ስራዎች ቀርበው በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎባቸዋል። በዚህም ዳሰሳ ጥናቱ የአካባቢው ማህበረሰብ አማራጭ የመረጃ ምንጭ እንደሚፈልግ የሚያሳይ እንደሆነና ሬድዮ ጣብያው ሊከፈት መታቀዱም ከልብ እንደሚደግፉት እና ለተግባራዊነቱም ከዩኒቨርሲቲው ጎን ቆመው ድጋፋቸው እንደሚያሳዩ  በውይይቱ ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የመገናኛ ብዙሀን የምዝገባና ፍቃድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ ሲሳይ በበኩላቸው በሌሎች መገናኛ ብዙሃን የማይሸፈኑ የአካባቢያዊ መረጃዎችን ለማህበረሰቡ በማድረስ የማህበረሰቡን ወግ ፣ ባህልና ቋንቋ ለማሳደግ እንዲሁም የአካባውን የቱሪዝም መዳረሻዎች ለማስተዋወቅ የማህበረሰብ ሬድዮ ድርሻ የጎላ ነው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የአከባቢው ማህበረሰብ መረጃዎች በቀላሉ የሚለዋወጡበት እና ጥቅማቸውን ለማስከበር እንዲነሳሱ የሚያስችላቸውን መድረክ ስለሚፈጥር የማህበረሰብ ሬዲዮ ሚና የላቀ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

በጉባኤው ላይ የተሳተፉ የማህበረሰብ ተወካዮች በበኩላቸው አክሱም ዩንቨርሲቲ የማህበረሰብ ሬድዮው ጣብያው ለማቋቋም ላሳየው ተነሳሽነት አድንቀዋል፡፡ ከሽረ ከተማ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ የተወከሉት አቶ ገብረኪዳን በርሀ እና በአክሱም ዩንቨርሲቲ የሴቶች እና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ባለሙያ ወ/ሮ ዝናብ ሓጎስ  እንደገለፁት የማህበረሰብ ሬድዮ ጣቢያው መቋቋም የአካባቢውን ማህበረሰብ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መረጃ እንዲያገኙ ከማገዙም ባለፈ ወጣቶችና ሴቶች በአካባቢያቸው ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ያበረታታል ብለዋል

የማህበረሰብ ተኮር የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ሬድዮ ጣብያው የሚቀሩትን ስራዎች በማጠናቀቅ በቀጣይ አመት ሙሉ ለሙሉ ስራውን ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡