ዩንቨርሲቲው የሀገሪቱን ልማት የሚደግፉና የህብረተሰቡን ችግሮች የሚቀርፉ ጥናትና ምርምሮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው

አክሱም ዩንቨርሲቲ የሀገሪቱን ልማት የሚደግፉና እና የህብረተሰቡን ችግሮች ሊቀርፉ የሚችሉ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን በአክሱም ዩንቨርሲቲ የምርምር እና የድህረ ምረቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር  ዶ/ር ሙሉጌታ በሪሁ ገለፁ::

ዳይሬክተሩ ይህንን ያሉት ‘አክሱም ዩኒቨርሲቲ በጥናትና ምርምር ሃገራዊ እድገትን ለመደገፍ የሚኖረው ሚና’ በሚል መሪ ቃል ሁለተኛው የአክሱም ዩንቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ ከታህሳስ 19-20 ዓ.ም በተካሄደበት ጊዜ ነው፡፡ በኮንፈረንሱ የህግ ፣ የቱሪዝም ፣ የአርኪሎጂ ፣ የኢኮኖሚ እና የግብርና ርዕሰ ጉዳዮችን የሚዳስሱ 20 ጥናትና ምርምር ቀርበዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ኮንፈረንሱ ለዩንቨርሲቲዉ መምህራን የእዉቀት ሽግግርን ከመፍጠር ባለፈ ዩኒቨርሲቲዉ የሀገሪቱን ልማት ሊደግፉ እና የህብረተሰቡን ችግሮች ሊቀርፉ የሚችሉ ወጣት ተመራማሪዎችን ለማፍራት ጠቀሜታዉ የጎላ ነው፡፡

በኮንፈረንሱ ከቀረቡት የጥናትና ምርምር  ፅሁፎች በተጨማሪ ወይይት እና ግምገማ ተካሂዶባቸዉ ወደ ህብረተሰቡ ወርደዉ ጠቀሜታ የሚሰጡበት መንገድ እንደሚመቻችም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

ለዚህ ማሳያም ከዚህ ቀደም ዩንቨርሲቲዉ በወልቃይት ስኳር ፋብሪካ የስኳር አገዳ መስኖ ልማት ስራ እና የቱሪስቶችን ቆይታ በማራዘም ዙሪያ ላይ የተሰሩ ጥናትና ምርምሮች  ወደ ተግባር ቀይሮ ስኬታማ ስራ መስራቱን ዳይሬክተሩ አሰታዉሰዋል::

እንደ ጥናትና ምርምር  አቅራቢዎቹ ገለፃ ዩንቨርሲቲው ይህ ኮንፈረንስ ማዘጋጀቱ አቅማቸዉን ለማሳደግ እና በሙያቸው አገራቸዉን ለማበልፀግ መድረኩ የላቀ አሳተዋፅኦ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡

ምርምርና ጥናታቸውን ካቀረቡት መካከል የህግ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አቶ ስለኣምላክ የማነ ኢትየጵያ አለም አቀፍ የንግድ ደንበኞቿን እንዴት መጠበቅ እና ከለላ መስጠት አለባት በሚል ርዕስ ፅሁፋቸዉን አቅርበዋል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ አለም አቀፍ የንግድ ተቋም አባል ከሆነች በርካታ አለም አቀፍ ድርጅቶች በቀላሉ ወደ አገሪቱ ይገባሉ፡፡ በመሆኑም ጥናቱ ወደ ሀገሪቱ የሚገቡ አለም አቀፍ የንግድ ድርጅቶች እንዴት የደንበኞቿን መብት መጠበቅ እንዳለባት የሚያሳይ  ነው፡፡

በተጨማሪም በጤና ሳይንስ ኮሌጅ የፋርማሲ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አቶ ገብረ ተክለማርያም ተላላፊ ባልሆኑ እስከ ህይወት ፍፃሜ ድረስ አብረዉ የሚቆዩ እና ታክመዉ መዳን በማይችሉ ነገር ግን ልንቆጣጠራቸዉ በምንችላቸዉ እንደ ስኳር ባሉ በሽታዎች የመድሐኒት አጠቃቀም ላይ ጥናታዊ ፁሁፋቸዉን አቅርበዋል:: እንደ አቶ ገብረ ገለፃ የስኳር በሽታን በአግባቡ አለመቆጣጠር እንደ ደም ግፊት፣ ኩላሊት፣ ነርቭ እና ከአይን ጋር ለተያያዙ ከባድ በሽታዎች ይዳርጋል::

በኮንፈረንሱ የሴቶች ተሳትፎ አናሳ መሆኑንና በቀጣይ ወጣት ሴት ተመራማሪዎችን በተሻለ መልኩ ማሳተፍ እና ማበረታት እንደሚገባም የተገለፀ ሲሆን ዩንቨርሲቲው ተመሳሳይ ኮንፈረንሶች በየጊዜዉ በማዘጋጀት በጥናትና ምርምር  ዘርፍ የመምህራን ተሳትፎና አቅም  ለማሳደግ ይበልጥ መስራት እንዳለበትም ተሳታፊዎች ጠቁመዋል::