አክሱም ዩኒቨርሲቲ ለተቸገሩ ተማሪዎች የትምህርት እና የንፅህና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

አክሱም፣ ነሐሴ 25/2018 ዓ.ም (አክሱም ዩኒቨርሲቲ) አክሱም ዩኒቨርሲቲ ከላዕላይ ማይጨው ወረዳ እና ከአክሱም ከተማ ከሚገኙ 12 አብያተ ትምህርት ለተውጣጡ 100 (50 ወንዶች እና 50 ሴቶች) አቅም የሌላቸው ተማሪዎች የትምህርት እና የንፅህና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ። በድጋፍ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአክሱም ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር እና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንትና የፕሬዚዳንት ተወካይ ዶክተር አብርሃም ነጋሽ እንደገለፁት፤ ድጋፉ የትምህርት ሚኒስቴር “ህብር በተግባር፤ አንድ ተማሪ – አንድ ተስፋ” በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀውን የህብር ቀን ምክንያት በማድረግ የተደረገ ነው ብለዋል። ጨምረው ብዝሃነት እንደ ውበትና ጥንካሬ በመውሰድ አብሮነትን፣ መተሳሰብን እና የጋራ ነገን በተግባር ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልፀው፣ የትምህርት ተቋማትም ድጋፍ የሚሹ ተማሪዎችን ለአዲሱ የትምህርት ዘመን የሚያስፈልጓቸውን ቁሳቁሶች ማሟላት እንዳለባቸው አሳስበዋል። የማዕከላዊ ዞን የማህበራዊ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ በርሀ ገብሪሃንስ እና የአክሱም ከተማ ትምህርት ፅህፈት ቤት ኃላፊ መምህር ክብሮም ኃይለስላሴ በበኩላቸው፤ የተደረገው ድጋፍ ዩኒቨርሲቲው ቀደም ሲል ሲያደርጋቸው የነበሩ የማህበረሰብ አግልግሎቶችን የሚያስቀጥል መሆኑን ገልፀዋል ። መሰል እገዛዎች ተጠናክረው በመቀጠል እድሉን ያላገኙ ሌሎች ተማሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመው፣ ድጋፍ የተደረገላቸው ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ ወላጆች አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። በመጨረሻም የአክሱም ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር በርሀ ታፈረ፤ ድጋፉ ተማሪዎችን ለማበረታታት ያለመ መሆኑን ጠቁመው፣ ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰቡን ችግሮች ለመፍታት እና አቅሙ በፈቀደ መጠን ድጋፍ ለማድረግ ሁልጊዜም ከህዝቡ ጎን እንደሚቆም አረጋግጠዋል።

ልህቀት በጥረት!

አክሱም ዩኒቨርሲቲ

Written by