ልብ ሰባሪ ሃዘን !!

በአክሱም ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅና ኮምፕረሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስራ ባልደረባችን የነበሩ መምህር እና ተመራማሪ ረ/ፕሮፌሰር መብራህቱ አባይ ስዩም ያጋጠማቸው ድንገተኛ ህልፈተ-ሂወት አስደንጋጭ እና ልብ ሰባሪ ክስተት ነው።

የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን እየገልፅን ለባልደረባችን መንግስተ ሰማይ እንዲያዋርሳቸው እየተመኘን ለቤተሰቦቻቸው ፣ ለስራ ባልደረባቻቸው እንዲሁም ለጓደኞቻቸው መፅናናትን እንመኛለን። መብራህቱ ኣባይ ስዩም በዩኒቨርሲቲያችን ከተራ መምህርነት እስከ አመራርነት የነበራቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ እና ሂወት ታሪካቸው በአጭሩ እንደሚከተለው ቀርቧል።

ረ/ፕሮፌሰር መብራህቱ አባይ ስዩም በማእከላይ ዞን ፣ ናዕዴር ወረዳ ፣ በ አበባ ዮውሃንስ ቀበሌ ከአባታቸው አቶ ኣባይ ስዩም እና ከእናታቸው ወ/ሮ ቅዱሳን ፍሰሃ ጥር 19 ፣1980 ዓ/ም ተወለዱ። ዕድሚያቸው ለትምህርት እንደደረሱ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት በአከባቢያቸው የሚገኘው በማሕበረ ዴጎ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና በአኽሱም አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርታቸው አጠናቋል።

የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በጤና መኮነን(Health Officer) ፣ የሁለተኛ ዲግሪያቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በህብረተሰብ ጤና-ኢፒደሞየሎጂ(Master of Public Health(MPH) in Epidemiology) ሞያ ተምረዋል።

ረ/ፕሮፌሰር መብራህቱ አባይ ስዩም በነበራቸው ከፍተኛ የትምህርት ውጤት መሰረት በ2004 ዓ/ም በአክሱም ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በአስተማሪነት እና ተመራማሪነት ተቀጥረው ሲያገለግሉ ቆይተዋል። በአመራርነት ደረጃ በዩኒቨርሲቲያችን ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በህብረተሰብ ጤና ትምህርት ክፍል ሓላፊ፣ የስልጠና ማእከል ኦፊሰር እንዲሁም የጤና ሳይንስ ኮሌጅና ኮምፕረሄንሲቭ ስፔሻላዝድ ሆስፒታል የምርምር እና ኣካዳሚክ ዳይሬክተር በመሆን ኣገልግለዋል።

በኣስተማሪነታቸው እና ተመራማሪነታቸው በአርኣያነት የሚታወቁ ባልደረባችን፣ ከ20 በላይ የጥናት ህትመቶች በታወቁ ጆርናሎች ያሳተሙ ሲሆኑ እስከ ህልፈተ-ሂወታቸው በታማኝነት እና በቅንነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

ረ/ፕሮፌሰር መብራህቱ አባይ ስዩም የጤና ሳይንስ ኮሌጅና ኮምፕረሄንሲቭ ስፔሻላዝድ ሆስፒታል የአካዳሚክና ምርምር ዋና ዳይሬክተር(Chief Academic and Research Director) ሆነው ሲሰሩ የኮረና በሽታ በመቆጣጠር እና በጦርነቱ ግዘ ለስራ ባልደረቦቻቸው ሰብኣዊ ድጋፍ እንዲያገኙ ያደረጉት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሲታወስ ይኖራል። በባልደረቦቻቸው እና ጓደኛቻቸው የተመሰገኑ፣ በስራ አፈፃፀማቸውም የላቁ አንደበተ ርቱእ እና ገና ለህብረተሰባቸውም ሆነ ለሞያቸው የሚተጉ ወጣት ምሁር ነበሩ።

ረ/ፕሮፌሰር መብራህቱ አባይ ስዩም በመቐለ ከተማ ስራ ላይ ሳሉ ለጊዜው ባልታወቀ ምክንያት በቀን 4 /12/2017 ዓ/ም በ 37 ዓመታቸው ለህልፈተ-ሂወት ተዳርገዋል። ረ/ፕሮፌሰር መብራህቱ አባይ ስዩም ባለ ትዳርና የአንድ ሴት ልጅ አባት ነበሩ።

የተሰማንን ጥልቅና መራራ ሀዘን እየገለጽን ለቤተሰቦቻቸው፣ ለስራ ባልደረባቸውና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ልባዊ መፅናናትን እንመኛለን!!

ነፍሳቸውን ፈጣሪ በአፀደ ገነት ያሳርፍልን!!

አክሱም ዩኒቨርሲቲ

Written by