አክሱም ዩኒቨርሲቲ ለ12ኛ ክፍል ማኅበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች ገለፃ አደረገ

አክሱም ዩኒቨርሲቲ፣ ሐምሌ 05/2018 ዓ.ም.

ከሐምሌ 6 እስከ ሐምሌ 8/2018 ዓ.ም. ድረስ በኮምፒውተር (CBT) አማካኝነት ለሚሰጠው የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና የሚቀመጡ ከ 700 በላይ አራተኛ ዙር የማኅበራዊ ሳይንስ ተፈታኞችን ዝግጁ ለማድረግ፤ ዩኒቨርሲቲው በፈተና አሰጣጥ ሥርዓትና ሕገ-ደንቦች ዙሪያ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ (ኦሬንቴሽን) መድረክ አዘጋጅቷል።

በመክፈቻ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና የፈተናው ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ገብረየሱስ ብርሃነ፣ ከአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙሉጌታ በሪሁ ጋር በመሆን ለተፈታኞቹ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። መሪዎቹ ተማሪዎቹን የሚያበረታታ የስነ-ልቦና ምክር የለገሱ ሲሆን፣ ፈተናው በሰላማዊና በስኬታማ ሁኔታ እንደሚጠናቀቅ ሙሉ እምነታቸውን ገልጸው፤ ተፈታኞችም የተቀመጡ መመሪያዎችን በአግባቡ እንዲያከብሩ አሳስበዋል።

በተጨማሪም በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የኤአይቲ (AIT) ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር እና የዩኒቨርሲቲው አገር አቀፍ ፈተናዎች አስተባባሪ ዶክተር መሃመድ አህመድ፤ ተፈታኞች በፈተና ወቅት በጥብቅ የተከለከሉ ቁሳቁሶችን ይዘው እንዳይገቡና ሊከተሏቸው ስለሚገቡ አጠቃላይ መመሪያዎች ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በትምህርት ሚኒስቴር የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ፈተና ማዕከል አስተባባሪ አቶ አለልኝ አሩቴ በበኩላቸው፣ እያንዳንዱ ተማሪ የፈተና መግቢያ (አድሚሽን) ካርድ እና ዲጂታል መታወቂያ መያዝ እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል። አክለውም፣ ተማሪዎች በራስ የመተማመን ስሜት ኖሯቸው የራሳቸውን ፈተና ብቻ እንዲሠሩና የኩረጃ ተግባርን በጽኑ እንዲጸየፉ በማሳሰብ የፈተናውን ሕግጋት አብራርተዋል።

የተማሪዎች አገልግሎት ዲን ጽሕፈት ቤት ምክትል ዲን መምህር ዘለዓለም ሓጎስ ተማሪዎች በቆይታቸው በመኝታ ክፍልና በመመገቢያ አዳራሽ አካባቢ ሊተገብሯቸው ስለሚገቡ የሥነ-ምግባር እሴቶች እና ሊወገዱ ስለሚገባቸው ድርጊቶች ጥልቅ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የቴክኒክ ዝግጁነትን በተመለከተ የውሂብ ጎታ (ዳታቤዝ) አስተዳዳሪው መምህር ብርሃኑ መብርሃቱ፣ ስለ ኦንላይን ፈተና አሰጣጥ ሂደት እና ስለ ኮምፒውተር አጠቃቀም ቴክኒካዊ ሁኔታዎች ለተፈታኞቹ ተግባራዊ ግንዛቤ አስጨብጠዋል።

አክሱም ዩኒቨርሲቲ የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ያለምንም የፀጥታና የቴክኒክ እንቅፋት በሰላም እንዲጠናቀቅ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅትና በትብብር እየሠራ ይገኛል።

ለአራተኛ ዙር የበይነመረብ (CBT) ማኅበራዊ ሳይንስ ተፈታኝ ተማሪዎቻችን በሙሉ መልካም ዕድልና ስኬትን እንመኛለን!

ልህቀት በጥረት!

አክሱም ዩኒቨርሲቲ

Written by 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *