አክሱም ዩኒቨርሲቲ፣ ጥቅምት 28/2018 ዓ.ም አክሱም ዩኒቨርሲቲ ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በማዘጋጀት ገለፃ ሰጥቷል። በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ገብረየሱስ ብርሃነ ለተማሪዎቹ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት አስተላልፈዋል። ፕሮፌሰር ገብረየሱስ ጨምረው ተማሪዎች እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፈው የመጡ በመሆናቸው ትምህርታቸውን በትጋት መከታተል እንደሚገባቸው አሳስበዋል። የተማሪዎች ህብረት ምክትል ፕሬዚዳንት ተማሪ ቴድሮስ ፅገ በበኩላቸው ለተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ካስተላለፈ በኃላ ፤ ተማሪዎቹ እዚህ ለመድረስ ያነበቡት የትምህርት መፃሕፍትን ብቻ ሳይሆን ህይወት የፈተነቻቸውን እጅግ በርካታ ውጣ ውረዶችና አስቸጋሪ መንገዶችን በማለፍ መሆኑን ገልፀዋል። በመድረኩ ላይ ተማሪዎች በመኝታ ክፍላቸው እና በመመገቢያ አዳራሽ ማድረግ የሚገባቸውንና የሌለባቸውን ጉዳዮች በተመለከተ በተማሪዎች አገልግሎት ፅ/ቤት ዲን ዶ/ር ሃፍቶም ከበደ ገለፃ የተደረገላቸው ሲሆን፤ ስለ ግል መረጃ (ባዮግራፊ) አሞላልና የምዝገባ ሂደት በሬጅስትራር ፅ/ቤት ተወካይና የሲስተም አድሚኒስትሬተር መ/ር መድሃንየ ካሕሱ፣ በመማር ማስተማር ሂደት ዙሪያ ማድረግ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች ደግሞ በፍሬሽማን አስተባባሪ መ/ር ተኽለ ገ/መድህን ማብራሪያ ተሰጥቷል። በመጨረሻም የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙሉጌታ በሪሁ የመዝጊያ ንግግር አድርገዋል። ዶ/ር ሙሉጌታ በንግግራቸው ተማሪዎች የአስራ ሁለት ዓመት ጉዟቸውን በስኬት አጠናቅቀው የማለፊያ ነጥብ በማምጣት የዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ህይወት መጀመራቸውን ጠቅሰው ፣ ዩኒቨርሲቲ የአስተሳሰብ ለውጥ፣ የፈጠራ ክህሎት እና የችግር አፈታት ዘዴ ማዕከል በመሆኑ የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የተሳካ እንዲሆን ታታሪነታቸው ወሳኝ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።
ልህቀት በጥረት!
አክሱም ዩኒቨርሲቲ






