አክሱም ዩኒቨርሲቲ — ሰኔ /2018 ዓ.ም
የአክሱም ዩኒቨርሲቲ የቴክስታይል እና ፋሽን ቴክኖሎጂ ፋኩሊቲ ዓድዋ ካምፓስ ፣ አዲስ የተደራጀ ለጋርመንት እና ፋሽን ዎርክሾፕ የሚሆኑ ማሽኖች በይፋ ስራ አስጀምሯል። ወደ ስራ የገቡት ዘመናዊ ማሽኖች የስፖርት ማልያና ሱሪዎችን ጨምሮ የተለያዩ አልባሳትን መስፋት የሚችሉ ሲሆን፣ በልብሶች ላይ ፅሑፎችንና ምስሎችን የሚያትሙ የፕሪንቲንግ እና የጥልፍ ማሽኖችንም ያካተቱ ናቸው።
በዎርክሾፑ የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ገብረየሱስ ብርሃነ፣ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙሉጌታ በሪሁ፣ የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር አብርሃም ነጋሽ፣ በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የAIT ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር መሀመድ አህመድ፣ የዓድዋ ካምፓስ የቴክስታይል እና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኃላፊ መምህርት ምሕረት ሃይለማርያም፣ እንዲሁም የኮሌጅ ዲኖችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
በዕለቱም የቴክስታይል እና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኃላፊ መምህርት ምሕረት ሃይለማርያም ባደረጉት ንግግር፣ የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት እነዚህን ውድና ጠቃሚ ማሽኖች ገዝቶ ወደ ስራ ለማስገባት ለወሰደው ቆራጥ ውሳኔና ላሳየው አመራር ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በአንጻሩ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ገብረየሱስ ብርሃነ እና ምክትል ፕሬዚዳንቶቹ በበኩላቸው፣ መምህርት ምሕረት ሃይለማርያም እነዚህን ትላልቅ ማሽኖች በማስገባትና ዎርክሾፑን ወደ ስራ ለማስገባት ላደረጉት ከፍተኛ ጥረትና ላሳዩት የስራ ተነሳሽነት አድናቆታቸውን ችረዋል።
በማጠቃለያውም፣ እነዚህ ዘመናዊ ማሽኖች በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውሉ፣ ጥብቅ ክትትል እና እንክብካቤ እንዲደረግላቸው እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች እና ማህበረሰብ ባለፈ ለአካባቢው ነዋሪዎች ጠቃሚ የሆኑ አጫጭር ስልጠናዎችን በመስጠት ስራ እንዲፈጥሩ እንደሚገባ በአጽንኦት ተገልጿል።
ልህቀት በጥረት!
አክሱም ዩኒቨርሲቲ

