አክሱም ዩኒቨርስቲ ሚያዝያ 5 ቀን 2018 ዓ.ም
በአክሱም ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅና ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል (CHS-CSH) ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ እድሳት ሲደረግለት የቆየው የፅኑ ሕሙማን መታከሚያ ክፍል (ICU) ግንባታው ተጠናቆ ዛሬ በደመቀ ሁኔታ ተመርቋል።
በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ገብረየሱስ ብርሃነ፣ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ኃላፊ ዶ/ር ገብረሂወት ተክለሃይማኖት፣ እንዲሁም ከፍተኛ የሥራ አመራሮችና ኃላፊዎች፣ የኮሌጁ አመራሮች (ዶ/ር አብርሃም ነጋሽ፣ ዶ/ር መኮንን አረጋይ፣ ዶ/ር መሐመድ አሕመድ፣ ዶ/ር ሃፍቶም ከበደ እና አቶ ፍረሰናይ አበራ) ተገኝተዋል።
የታደሰው የፅኑ ሕሙማን ክፍል ዘመናዊ አሰራርን የተከተለ ሲሆን ክፍሉ ለሕፃናትና ለአዋቂዎች ተብሎ የተከፋፈለ ሲሆን ፤በተጨማሪም ለእያንዳንዱ አልጋ የቀጥታ የኦክስጅን መስመር ዝርጋታ ተገጥሞለታል።
ዶ/ር ገብሪሂወት ተክለሃይማኖት እንደገለጹት፣ ክፍሉ አስፈላጊው የሕክምና መሣሪያዎች፣ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይልና የውሃ አቅርቦት ተሟልቶለት ከዛሬ ጀምሮ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
የመስክ ምልከታና የቀጣይ ፕሮጀክቶች ሁኔታ
ከምረቃው በኋላ አመራሮቹ በሆስፒታሉ ግቢ ውስጥ የሚገኙ የኦክስጅን ማምረቻ ክፍልን፣ የመድኃኒት መጋዘን እና ቤተ-መጻሕፍትን ጎብኝተዋል። በተጨማሪም በግንባታ ሂደት ላይ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ማለትም ልዩ የሕክምና ክሊኒክ፣ የኩላሊት እጥበት ማዕከል፣ ባለብዙ ዘርፍ የሪፈራል ሆስፒታል( Tertiary Hospital) ሕንፃ እና የሠራተኞች መዝናኛ ክበብ ያሉበት ደረጃ ተገምግሟል። የኮንስትራክሽን ኃላፊው አቶ ፍረሰናይ አበራ እነዚህ ግንባታዎች በቅርቡ ተጠናቅቀው ወደ ሥራ እንደሚገቡ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
ተግዳሮቶችና የፕሬዝዳንቱ መልእክት
የኮሌጁ አመራሮች በተከናወነው ሥራ ደስተኞች መሆናቸውን ቢገልጹም፣ ለቀጣይ መፍትሄ የሚሹ ነጥቦችንም አንስተዋል። ከእነዚህም መካከል በሴት ተማሪዎች መኝታ ክፍል የሚታየው የውሃ እጥረት፣ በኦክስጅን ማምረቻ ክፍሉ ያለው የባለሙያዎች እጥረት፣ እንዲሁም የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ችግር ዋነኞቹ ናቸው።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ገብረየሱስ ብርሃነ ባስተላለፉት መዝጊያ ንግግር፣ ፕሮጀክቱ ለምረቃ የበቃው በከፍተኛ ክትትልና ጥረት መሆኑን ገልጸዋል። ቀሪ ሥራዎችን በፍጥነት ለማጠናቀቅና ጥራት ያለው አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ጠንካራ ቁርጠኝነት (Commitment) እና ቀጣይነት ያለው ክትትል (Follow-up) እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
ኣክሱም ዩኒቨርስቲ!




